ሰቆቃወ ጰጥሮስ
አየ ምነው እመ
ብርሀን? ኢትዮጵያን ጨከንሽባት?
ምነው ቀኝሽን
ረሳሻት?
እስከመቼ ድረስ
እንዲሁ መቀነትሽን ታጠብቂባት?
ልቦናሽን ታዞሪባት?
ፈተናዋን ሰቀቀንዋን
ጣሯን ይበቃል ሳትያት?
አላንቺ እኮ ማንም
የላት....
አውሮጳ እንደሁ
ትናጋዋን በፋሽስታዊ ነቀርሳ
ታርሳ ተምሳ በስብሳ
ሂትለራዊ እባጭ
ጫንቃዋን እንደ ኮረብታ ተጭኗት
ቀና ብላ እውነት
እንዳታይ አንገቷን ቁልቁል ጠምዝዟት
ነፍሷን ድጦ ያስበረከካት
ስልጡን ብኩን
መጻጉዕ ናት፤...
እና ፈርቼ እንዳልባክን
ሲርቀኝ የኃይልሽ ውጋጋን
አንቺ ካጠገቤ
አትራቂ በርታ በይኝ እመብርሀን
ቃል ኪዳኔን እንዳልረሳት
እንዳልዘነጋት ኢትዮጵያን::
አወን ብቻየን
ነኝ ፈራሁ
እሸሸግበት ጥግ
አጣሁ
እምፀናበት ልብ
አጣሁ
እማማ ኢትዮጵያ
መንፈሴ ተፈትቶ እንዳይከዳት ሰጋሁ::
አዋጅ የምስራች
ብዬ የትብት ምግቤን ገድፌ
ከናቴ ማህጸን
አልፌ
በኢትዮጵያ ማህጸን
አርፌ
ከአፈርዋ አጥንቴን
ቀፍፌ
ደሜን ከደሟ አጠንፍፌ
ከወዟ ወዜን ቀፍፌ
ብህጻን እግሬ
ድኼባት በህልም አክናፍ ከንፌ
እረኝነቴን በሰብሏ
ብምድሯ ላብ አሳልፌ
ከጫጩትና ከጥጃ
ከግልገል ጋር ተቃቅፌ
በጋው የእረኛ
አደባባይ ክረምት እንደወንዙ ፍሳሽ
በገጠር የደመና
ዳስ በገደል ሸለቆ አዳራሽ
ከቆቅና ከሚዳቋ
ከዥግራ ጠረን ስተሻሽ
በወንዝ አፋፍ
ሀረግ ዝላይ መወርወር መንጠልጠል ጢሎሽ
ከፍልፈል ጋር
ሩጫ ስገጥም ከቀበሮ ድብብቆሽ
ከናዳ ጫፍ ሳር አጨዳ ለግት ላሜ ትንሽ ግጦሽ
ለጥጃዬ የሌት
ግርዶሽ
ለጥማድ በሬዎች
ራት ለማታቸው ትንሽ ድርቆሽ
ለግልገሌ ካውሬ
ከለል
እማሳው ሥር ጎጆ
መትከል
ለፀሐይ የሾላ
ጠለል ለዝናብ የገሳ ጠለል
ውሎ የንብ ቀፎ
ማሰስ ያበባ እምቡጥ ሲፈነዳ
ግጦሽ ሣር ሲለመልም
ሲሰማሩ ሰደድ ሜዳ
አዝመራው ጣል
ከንበር ሲል ከብቱ ለሆራ ሲነዳ
ፈረስ ግልቢያ
ስሸመጥጥ ከወፎች ዜማ ስቀዳ
ልቤ በንፋስ ተንሳፎ
በዋሽንት ዋይታ ሲከዳ
ያቺን ነው ኢትዮጵያ
የምላት
እመ ብርሃን እረሳሻት?
ያችን የልጅነት
ምስራች? የህጻንነት ብሥራት
የሣቅ የፍንደቃ
ዘመን የምኞት የተስፋ ብጽዓት
ያቺን የልጅነት
እናት?
አዛኚቱ እንዴት
ብለሽ ጥርሶችሽን ትነክሽባት?
ስሜን በስምሽ
ሰይሜ ባገልግሎትሽ ስዋትት
ከዜማ ቤት እቅኔ
ቤት ከድጓ ቤት እመጽሐፍት
ካንቺ ተቆራኝታ
እድሌ ካንቺ ተቆራኝታ ነፍሴ
ከቀፈፋ ደጀ ሰላም
ከቤተልሄም ቅዳሴ
አኮ ቀዶ ቀፎ
ዳባ ለብሶ
ቅኔ ዘርፎ ግሥ
ገሦ
መቅደስ አጥኖ
ማህሌት ቆሞ
በልብሰ ተክህኖ
አጊጦ በብር አክሊል ተሸልሞ
እመ ብርሀን ያንቺ
ጽላት ነፍሴ ላይ በሳት ታትሞ
የመናኒው ያባ
ተድላ ረድ ሆኜ አብሮኝ ታድሞ
ሕይዎቴ እምነትሽን
ጸንሶ
ሥጋ ፈቃዴ ተድሶ
ለሕንጻሽ መዲና
ቆሞ ለክብርሽ ድባብ ምሰሶ
ስሜን በስምሽ
ሰይሜ ሆነሽኝ የእምነቴ ፋኖስ
ለዋዜማሽ ግሸን
ማርያም ለክብርሽ ደብረ ሊባኖስ
ስሮጥ በወንበሩ
አኖርሺኝ በአንበሳው በቅዱስ ማርቶስ
ታዲያን ዛሬ ኢትዮጵያ
ስትወድቅ ከምትሰጪኝ ለፍርሀት ጦስ
ምነው በረኝነት
እድሜ ዓይኔን በጓጎጣት የሎስ
የጋኔል ጥንብ
አንሳ ከንፎ ወርዶ በጨለማ በርኖስ::
ባክሽ እመብርሀን
ይብቃሽ ባክሽ ምስለ ፍቁር ወልዳ
ጽናት ስጪኝ እንድካፈል
የእናቴን የኢትዮጵያን ፍዳ
ከነከሳት መርዝ
እንድቀምስ ከነደደችበት እቶን
የሷን ሞት እኔ
እንድሞታት ገላዋ ገላዬ እንዲሆን::...
አዎን ብቻዬን
ነኝ ፈራሁ
እምፀናበት ልብ
አጣሁ
እሸሸግበት ጥግ
አጣሁ::
ሕጻን ሆኜ የእርግብ
ጫጩት አንዳንዴ ራብ ሲያዳክማት
ችጋር ከጎጆዋ
ገፍቶ እዛፍ ግርጌ ሲጥላት
እናቷ በርራ ደርሳላት
በአክናፏ ሙቀት
ታቅፋት
እፍ እያለች ግንባሯ
ላይ ሕይወት ስትተነፍስባት
ወዲያው ነፍስ
ትዘራለች
ሽር ብር ትር
እያለች::
ባክሽ አንቺም
አትራቂብኝ
እመ ብርሃን እናቴ
ትንፋሽሽን እፍ በይብኝ
ጽናትሽን እፍ
በይብኝ
ወይም ይቺን የሞት
ጽዋ ጥላዋ ነፍሴን ካፈናት
እንዳልጠጣት አሳልፊያት
መራራ ክንፏን
ገንጥለሽ ቀጠሮ ቃልዋን ግደፊያት
አለዚያም ጽናትሽን
ስጪኝ ልጠጣው ኪዳነ ውሉን
የኔ ፍቃድ እምነትሽ
ነው ያንቺ ፍቃድ ብቻ ይሁን::
እንደ ጳውሎስ
እንድጸና በፍርሀት እንዳልታሰር
በውስጤ ከሚታገለኝ በሥጋ አውሬ እንዳልታወር
ለዕየለቱ ሞት
እንዳልሰንፍ
የኪዳኔ ቃል እንዳይነጥፍ
ቃልሽ በህሊናዬ
ዲብ ኃይልሽ ብህዋሴ ይረፍ::
ፍርሀት ቢያረብብኝም
አንቺ ካለሽ አልሰጋም
ኩርትም ብዬ እችልበት
እሸሸግበት አይጠፋም
የግማደ መስቀሌን
ጉጥ እታገስበት አላጣም
አለዚያማ ብቻዬን
ነኝ ኢትዮጵያም አላንቺ የላት
አንቺ አጽኝኝ
እንድጸናላት::
አስርጪብኝ የእምነት
ቀንጃ ለሥጋቴ አጣማጅ አቻ
ለጭንቀቴ መቀነቻ::
አወን ብቻዬን
ነኝ ፈራሁ
እሸሸግበት ጥግ
አጣሁ እምጸናበት ልብ አጣሁ....
፲፱፻፷፩ ቀበና
( ጸጋዬ ገብረ መድህን )