Saturday, June 23, 2018

ውድ የኢትዮ ጥበብ ገጽ ተከታታዮች ላለፉት ጥቂት አመታት ከማህበራዊ ድረ ገጽም ሆነ ከ ብሎጎቻችን ርቀን የነበረ ሲሆን ከአሁን በኋላ ግን እናንተን በንቃት ለማዝናናት ቃል እንገባላችኋለን:: 

የኢትዮ ጥበብ ቲም

Wednesday, August 14, 2013

ሰቆቃ ወ ጴጥሮስ

     ሰቆቃወ ጰጥሮስ


አየ ምነው እመ ብርሀን?  ኢትዮጵያን ጨከንሽባት?
ምነው ቀኝሽን ረሳሻት?
እስከመቼ ድረስ እንዲሁ መቀነትሽን ታጠብቂባት?
ልቦናሽን ታዞሪባት?
ፈተናዋን ሰቀቀንዋን ጣሯን ይበቃል ሳትያት?
አላንቺ እኮ ማንም የላት....
አውሮጳ እንደሁ ትናጋዋን በፋሽስታዊ ነቀርሳ
ታርሳ ተምሳ በስብሳ
ሂትለራዊ እባጭ ጫንቃዋን እንደ ኮረብታ ተጭኗት
ቀና ብላ እውነት እንዳታይ አንገቷን ቁልቁል ጠምዝዟት
ነፍሷን ድጦ ያስበረከካት
ስልጡን ብኩን መጻጉዕ ናት፤...
እና ፈርቼ እንዳልባክን ሲርቀኝ የኃይልሽ ውጋጋን
አንቺ ካጠገቤ አትራቂ በርታ በይኝ እመብርሀን
ቃል ኪዳኔን እንዳልረሳት እንዳልዘነጋት ኢትዮጵያን::
አወን ብቻየን ነኝ ፈራሁ
እሸሸግበት ጥግ አጣሁ
እምፀናበት ልብ አጣሁ
እማማ ኢትዮጵያ መንፈሴ ተፈትቶ እንዳይከዳት ሰጋሁ::
አዋጅ የምስራች ብዬ የትብት ምግቤን ገድፌ
ከናቴ ማህጸን አልፌ
በኢትዮጵያ ማህጸን አርፌ
ከአፈርዋ አጥንቴን ቀፍፌ
ደሜን ከደሟ አጠንፍፌ
ከወዟ ወዜን ቀፍፌ
ብህጻን እግሬ ድኼባት በህልም አክናፍ ከንፌ
እረኝነቴን በሰብሏ ብምድሯ ላብ አሳልፌ
ከጫጩትና ከጥጃ ከግልገል ጋር ተቃቅፌ
በጋው የእረኛ አደባባይ ክረምት እንደወንዙ ፍሳሽ
በገጠር የደመና ዳስ በገደል ሸለቆ አዳራሽ
ከቆቅና ከሚዳቋ ከዥግራ ጠረን ስተሻሽ
በወንዝ አፋፍ ሀረግ ዝላይ መወርወር መንጠልጠል ጢሎሽ
ከፍልፈል ጋር ሩጫ ስገጥም ከቀበሮ ድብብቆሽ
ከናዳ  ጫፍ ሳር አጨዳ ለግት ላሜ ትንሽ ግጦሽ
ለጥጃዬ የሌት ግርዶሽ
ለጥማድ በሬዎች ራት ለማታቸው ትንሽ ድርቆሽ
ለግልገሌ ካውሬ ከለል
እማሳው ሥር ጎጆ መትከል
ለፀሐይ የሾላ ጠለል ለዝናብ የገሳ ጠለል
ውሎ የንብ ቀፎ ማሰስ ያበባ እምቡጥ ሲፈነዳ
ግጦሽ ሣር ሲለመልም ሲሰማሩ ሰደድ ሜዳ
አዝመራው ጣል ከንበር ሲል ከብቱ ለሆራ ሲነዳ
ፈረስ ግልቢያ ስሸመጥጥ ከወፎች ዜማ ስቀዳ
ልቤ በንፋስ ተንሳፎ በዋሽንት ዋይታ ሲከዳ
ያቺን ነው ኢትዮጵያ የምላት
እመ ብርሃን እረሳሻት?
ያችን የልጅነት ምስራች? የህጻንነት ብሥራት
የሣቅ የፍንደቃ ዘመን የምኞት የተስፋ ብጽዓት
ያቺን የልጅነት እናት?
አዛኚቱ እንዴት ብለሽ ጥርሶችሽን ትነክሽባት?
ስሜን በስምሽ ሰይሜ ባገልግሎትሽ ስዋትት
ከዜማ ቤት እቅኔ ቤት ከድጓ ቤት እመጽሐፍት
ካንቺ ተቆራኝታ እድሌ ካንቺ ተቆራኝታ ነፍሴ
ከቀፈፋ ደጀ ሰላም ከቤተልሄም ቅዳሴ
አኮ ቀዶ ቀፎ ዳባ ለብሶ
ቅኔ ዘርፎ ግሥ ገሦ
መቅደስ አጥኖ ማህሌት ቆሞ
በልብሰ ተክህኖ አጊጦ በብር አክሊል ተሸልሞ
እመ ብርሀን ያንቺ ጽላት ነፍሴ ላይ በሳት ታትሞ
የመናኒው ያባ ተድላ ረድ ሆኜ አብሮኝ ታድሞ
ሕይዎቴ እምነትሽን ጸንሶ
ሥጋ ፈቃዴ ተድሶ
ለሕንጻሽ መዲና ቆሞ ለክብርሽ ድባብ ምሰሶ
ስሜን በስምሽ ሰይሜ ሆነሽኝ የእምነቴ ፋኖስ
ለዋዜማሽ ግሸን ማርያም ለክብርሽ ደብረ ሊባኖስ
ስሮጥ በወንበሩ አኖርሺኝ በአንበሳው በቅዱስ ማርቶስ
ታዲያን ዛሬ ኢትዮጵያ ስትወድቅ ከምትሰጪኝ ለፍርሀት ጦስ
ምነው በረኝነት እድሜ ዓይኔን በጓጎጣት የሎስ
የጋኔል ጥንብ አንሳ ከንፎ ወርዶ በጨለማ በርኖስ::
ባክሽ እመብርሀን ይብቃሽ ባክሽ ምስለ ፍቁር ወልዳ
ጽናት ስጪኝ እንድካፈል የእናቴን የኢትዮጵያን ፍዳ
ከነከሳት መርዝ እንድቀምስ ከነደደችበት እቶን
የሷን ሞት እኔ እንድሞታት ገላዋ ገላዬ እንዲሆን::...
አዎን ብቻዬን ነኝ ፈራሁ
እምፀናበት ልብ አጣሁ
እሸሸግበት ጥግ አጣሁ::
ሕጻን ሆኜ የእርግብ ጫጩት አንዳንዴ ራብ ሲያዳክማት
ችጋር ከጎጆዋ ገፍቶ እዛፍ ግርጌ ሲጥላት
እናቷ በርራ ደርሳላት
በአክናፏ ሙቀት ታቅፋት
እፍ እያለች ግንባሯ ላይ ሕይወት ስትተነፍስባት
ወዲያው ነፍስ ትዘራለች
ሽር ብር ትር እያለች::
ባክሽ አንቺም አትራቂብኝ
እመ ብርሃን እናቴ ትንፋሽሽን እፍ በይብኝ
ጽናትሽን እፍ በይብኝ
ወይም ይቺን የሞት ጽዋ ጥላዋ ነፍሴን ካፈናት
እንዳልጠጣት አሳልፊያት
መራራ ክንፏን ገንጥለሽ ቀጠሮ ቃልዋን ግደፊያት
አለዚያም ጽናትሽን ስጪኝ ልጠጣው ኪዳነ ውሉን
የኔ ፍቃድ እምነትሽ ነው ያንቺ ፍቃድ ብቻ ይሁን::
እንደ ጳውሎስ እንድጸና በፍርሀት እንዳልታሰር
 በውስጤ ከሚታገለኝ በሥጋ አውሬ እንዳልታወር
ለዕየለቱ ሞት እንዳልሰንፍ
የኪዳኔ ቃል እንዳይነጥፍ
ቃልሽ በህሊናዬ ዲብ ኃይልሽ ብህዋሴ ይረፍ::
ፍርሀት ቢያረብብኝም አንቺ ካለሽ አልሰጋም
ኩርትም ብዬ እችልበት እሸሸግበት አይጠፋም
የግማደ መስቀሌን ጉጥ እታገስበት አላጣም
አለዚያማ ብቻዬን ነኝ ኢትዮጵያም አላንቺ የላት
አንቺ አጽኝኝ እንድጸናላት::
አስርጪብኝ የእምነት ቀንጃ ለሥጋቴ አጣማጅ አቻ
ለጭንቀቴ መቀነቻ::
አወን ብቻዬን ነኝ ፈራሁ
እሸሸግበት ጥግ አጣሁ እምጸናበት ልብ አጣሁ....
፲፱፻፷፩ ቀበና ( ጸጋዬ ገብረ መድህን )



Sunday, June 23, 2013

በዛብህ ከ" ግጥም እና እኔ "

በዛብህ
እናትና አባቴ በስለት ወልደውኝ
ለስለታቸው መልስ ለካህኑ ሰጡኝ
የሰጣቸው ጌታ ከቅይሩ ሊያኖረኝ
ባካባቢው ካህናት ቅኔን አስተማረኝ
አሐዱ አምላክ ብዬ ዳዊቴን ደግሜ
ሰዓታት ወረቡን ቅዳሴውን ቆሜ
በለጋው ዕድሜዬ ጥበብን ተክኜ
ላፈሩኝ ወላጆች ከልብ ለተሳሉት
ላያዩኝ ላይድሩኝ መልሰው ለሰጡት
ለነሱ አልሆን ብዬ ከሱ ተጠግቼ
እንደ ጧፍ በራሁኝ ታየሁኝ ጎልቼ
የኔ ጎልቶ መውጣት ስለቱን ፈተነው
የውስጤን ሊለካ አየኝ ፊት አውራሪው
ከጌታው መኖሪያ ከባለፀጋው ቤት
አለች እፀ በለስ ነብሴ የምትሰጋት
ውበትዋያማረ ሰብል ነው እኔ የማልነካው
ባለፍኩበት ቁጥር ውስጤን ከስር የሚያናጋው
ፊደል ባስቆጠርኩኝ እንዳባቷ ዛዝ
ታዝብኝ ጀመረች የፍቅርን ትኩሳት
እኔ የስለት ልጅ እሷ እፀ በለስ
ድሮ ተዘግቶብኝ ሁሉ ማይቀመስ
የአጥሩ መብዛት ከዘሮቿ ደጅ
ምንም ብንካጀል የለን አማላጅ
የሁለታችንም ልብ ነጎደ ሌላለም
እያወቅነው የስለቱን የጌታውን ሕመም
ለሕዝብ አልተመቸ ለፈጠረኝ ጌታ
ከቀዬ ሲያባረኝ የስለት ከርታታ
ዲማ ጊዮርጊስም እንቢ አለ ይኼንን መዋጋት
በለስ ጌታ የድሃ ሰው ስለት ክልክል የነገስታት
ፍቅሬ ቢጠና አገር አቆራርጦ
አፈናቅሎ ጣላት እሷን አስቆጥቶ
ገደልን ፈንቅለን ተርበን ተጠምተን
ስለትን እረግመን ሸሸን ነገሥታቱን
መቃብር ሊወርደው ፍቅረ መውደዳችን
ባላሰብነው መንገድ ባልጠፋበት ጊዜ
የፈጠረን ጌታ ለፍቅር ለሐዘን ኑዛዜ
ሰጠን ያችን ዕለት የመቃብር ፍቅር
ይዘነው እንድንሄድ ሁሉንም በክብር::

ሔለን ካሳግጥም እና እኔ” (2005)

Tuesday, June 18, 2013

ድጋፋችሁ አይለየን

ውድ የዚህ ድረገጽ ጎብኝወች ይህ ድር ጀማሪ እንደ መሆኑ መጠን ከእናንተ አስተያየት ይፈልጋል ስለዚህ ለድሩ እድገት ያላችሁን የ ሀሳብ ድጋፍ አትንፈጉን ብለን ለማሳሰብ እንወዳለን

Saturday, June 15, 2013

ምርጥ ምርጥ አባባሎች

ብሂ
ሌላ መንገድ በመፈለግ ጊዜህን አታጥፋ መንገድ በፊትህ ነው:: ተነስቶ መራመድ ያንተ ፋንታ
ነው::
/አውግሰጢኖስ
ልብህን ብሩህ አድርገው ዓለምን የምትመለከትበት መስኮት ነውና::”
ጆርጅ በርናርድ ሾው
ሕይወት ራሷን ላለመጣል ከምትቀይሳቸው አቅጣጫዎች በአንዱ ውስጥ ማለፍ የግድ ነው::”
ጥሩ ወይም መጥፎ የሚባል ነገር የለም፣ አስተሳሰባችን የሚፈጥረው እንጂ::”
ዊልያም ሺክስፒር
ለሌሎች ካላሰብንና የምንችለውን ካላደረግንላቸው ከደስታ ምንጮች አንዱን እንዳደረቅን
እንገንዘብ::” ሬይ ሊመን ዊልበት
ብዙ ሰዎች የሚደሰቱት ራሳቸውን ለደስተኝነት ባዘጋጁት መጠን ነው::”
አብርሃም ሊንከን
መፍራት ያለብን ራሱን ፍራቻን ብቻ ነው::”
ፍራንክሊን ሩዝቬልት
ጨለማን ሲረግሙ ከመኖር አንዲት ቁራጭ ሻማ መለኮሱ ይበጃል::”
ራልፍ ዋልደ ኢመርሰን
ፍርሃትህን ለራስህ በጉያህ ሸሽግ ወኔህን ግን ከሌሎች ጋር ተካፈል::”
ሮበርት ሉዊስ ስቲቭንሰን
ለራሱ በቂ ነገር እያለው በጋራ መጠቀምን የማይሻና በማኅበር ለመኖር እራሱን የማያስገድድ ሰው
ቢኖር ሰው ሳይሆን አውሬ መሆን አለበት::”
አርስቶትል
ዛሬ ቀን ከሚገጥምህ ነገር ጋር ራስህን ለማስማማት ታገል እንጂ እኔ እንደፈለግሁት ካልሆነ
አትበል::”
አብርሃም ሊንከን
አንድን ነገር በማወቅና በመረዳት መካከል ትልቅ ልዩነት አለ::”
ቻርለስ ካታሪንግ

ወርቃማው ህግ
ክርስትና
እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተም ደግሞ እንዲሁ
አድርጉላቸው ሕግም ነቢያትም ይህ ነውና:: (ማቴ 7÷12)
እስልምና
ለራሳችሁ የምትመኙትን ለሌሎችም እንዲሆን እስካልተመኛችሁ ድረስ በትክክል
አላመናችሁም:: (የነብዩ መሐመድ ተግባራትና ንግግሮች)
የአይሁዶች እምነት
አንተ የምትጠላውን ነገር በባልጀራህ ላይ አታድርግ ይህ ነው እግዚአብሔር
ለሙሴ የሰጠው ሕግ ሲጠቃለል:: (ሒላል ታልሙድ ሻባት 31)
የባሃኢ እምነት
በአንተ ላይ ሊጫንብህ የማትፈልገውን በሌላ ላይ አታድርግ በራስህም ላይ
እንዲደርስብህ የማትሻውን ለማንም አትመኝ:: (ባሀኡላህ)
ቡዲሂዝም
ራስህን የሚጎዳ የሚመስልህን ነገር በሌሎች ላይ አታድርግ::
ሒንዱዝም
አንተ ላይ ቢደረግ የሚያስከፋህ ከሆነ አንተም በሌሎች አታድርግ የተግባር ሁሉ
ማጠቃለያ ይህ ነውና:: (ማኅበራታ 51517)
ጃኒዝም
ማንም ሰው ለራሱ እንዲደረግለት የሚሻውን እርሱም እንዲሁም በዓለም ዙሪያ
ላሉ ፍጡራን ሁሉ ያድርግ:: (ማሃቪራ ሱትራክሪታንጋ)
ሲኪሂዝም
ለማንም ባይተዋር አይደለሁም ማንም ለእኔ ባይተዋር አይደለም የሁሉም ወዳጅ
ነኝ:: (ጉሩ ግራንትዝ ሳሂብ ፒጂ.1299)
ዩኒታሪያኒዝም
ሁላችንም አካል የሆነበትን የፍጥረታት አንድነትና ትስስር በጽኑ እንደግፋለን
እንዲሁም ልዩ አክብሮት እንዲሰጠው እንተጋለን:: (የዩኒታሪያን መርሆ)
ታኦዝም
ጎረቤትህ ሲያተርፍ አንተ እንዳገኘህ ቁጠር ጎረቤትህ ሲከስር አንተ እንዳጣህ
አድርገህ ውሰድ:: (ቲአይ ሻንካ ካንዩንግ ፒዮን 213-218)
ኮንፉሺያኒዝም
የመልካም ሥነ ምግባር መሠረት ማጠቃለያ የሆነ አንድ ቃል ነው እሱም
ሩህሩህ መሆን በአንተ ላይ ሊደረግ የማትፈልገውን በለሎች ላይ አታድርግ::
(ኮንፍሺየስ አናሌክትስ 15.23)
ዞሮአስትሬይኒዝም
አንተን የሚጎዳ ነገር ሁሉ በሌሎች ላይ አታድርግ:: (ሻያስት-ና-ሻያስት 13.29)
ኔቲቭ ስፒሪቹአሊቲ
የኛ ሕልውና የሚረጋገጠው የምድራችን ተፈጥሮ ይዞታ ሲጠበቅ ነው:: (ቺፍ ዳን ጆርጅ)


ኢንተርፌዝ ፒስ ቢዩልዲንግ ኢንሽየቲቭ