መቆያ


ከአለቃ ገብረሐና ቀልዶች
የጾም ወቅት ነው:: አለቃ ገብረሐና ደጃዝማች ወዳጃቸው ዘንድ
ተጋብዘው ይሄዳሉ:: የጎመን ወጥ ይቀርብናም እንደነገሩ ይጋበዛሉ::
ሆኖም ጎመኑ በደንብ አልበሰለ ኖሮ አለቃ ሆዳቸውን ይቆዝራቸዋል::
ከግብር መልስም ብርዱ ስላየለ እሳት በእንክርት ወደእልፍኙ ቀረበ:: ይሄኔ
አለቃ ወደ እሳቱ አምርተው በርጩማ ላይ ከተቀመጡ በኋላ ልብሳቸውን
ገለጥ አድርገው ሆዳቸውን እሳት ያሞቁ ጀመር:: ደጃዝማቹም በድርጊቱ
ተገርመው “ምነው ሆድዎን እሳት የሞቃሉ?” ቢሏቸው “ጌታዬ ጎመኔን
እያበሰልኩ ነው” አሏቸው::
ይህን የመሳሰሉትን ቀልዶች እያፈለቁ አገር ያሸነፉትን አባ ገብረሐናን
ለማዋረድም የንጉሣውያን ቤተሰቦችና መኳንንቱ አንድ ተንኮል ፈጠሩ::
አባ ገብረሐና ግብር ቀርበው እንደተቀመጡም እንደራባቸው መብላት፣
መጠጣት፣ እንደሚችሉ ሆኖም ወደ ውጭ መውጣት እንደማይፈቀድላቸው
ይነገራቸዋል:: የሚቀርብላቸው ምግብም ጨውና ቅመም የበዛበት ኖሮ በላይ
በላይ ቢጠጡ ሽንታቸው መጣ:: ጨነቃቸው፤ ጠበባቸው:: ጥቂት አሰቡና
በኋላ እቴጌይቱን ጠርተው፤ “እባክዎን በቁጥር ተጣልተናልና ዳኙን::
አምስት መቶና አምስት መቶ ስንት ነው?” ቢሏቸው “ሺነዋ!” በማለት
መለሱላቸው:: “እግዜር ይስጥልኝ እመቤቴ፤ እርስዎ ካዘዙኝማ ማለፊያ
ነው::” ብለው እየሳቁ ወደ መፀዳጃ ቤት ሄዱ::

አረፈ አይኔ ሐጎስ፤ አለቃ ገብረሐና አስቂኝ ቀልዶቻቸው፤ 1979

ገንዘብ ሳይከፍሉ ለሰዎች ሊያበረክቱ የሚችሉዋቸው ስጦታዎች
‹‹ትልቅ ነገር ማድረግ ቢያቅተን ከፍቅር ጋር ትንሽ ነገር ማድረግ አያቅተንም›› ይላሉ ማዘር ተሬዛ:: በዕለት ተዕለት ውሎአችን ዋጋ (ገንዘብ)
የማያስከፍሉ፤ ነገር ግን ለሰዎች እጅግ ዋጋ ያላቸውን ነገሮችን አንድ ያልታወቁ ጸሐፊ እንዲህ አስቀምጠዋቸዋል::
የመስማት ስጦታ
ሰዎች ስለጉዳያቸው ወይም ስለችግራቸው ሲያወጉ ከልብ መስማትን የመሰለ ስጦታ የለም:: ታዲያ ሳናቋርጣቸው፤ በሃሳብ ሌላ ቦታ ሳንሔድ ወይም ስለምንመልስላቸው መልስ ሳናሰላሰል መሆን አለበት:: ዝም ብሎ ከልብ ማዳመጥ ብቻ!
ፍቅር የማሳየት ስጦታ
ፍጹም ሳይሰስቱ ከልብ ሰዎችን በመጨበጥና በማቀፍ ለእነርሱ ያለዎትን ፍቅር፤ ትኩረትና አድናቆት ይግለጹላቸው::
የሳቅ ስጦታ
በየዕለቱ የሚገጥምዎትን አስደሳች ሁኔታዎች (ጽሑፎች፤ ፎቶዎች፤ ካርቱኖች) በመላክ ደስታዎን (ሳቅዎን) ለሰዎች ያካፍሉ፤ የሌሎችንም ደስታ ወይም ሳቅ እንዲሁ ይካፈሉ::
የጽሑፍ ስጦታ
ሰዎች ስላደረጉልዎ መልካም ነገር ምስጋናዎን በራስዎ የእጅ ጽሑፍ በመጻፍ ይስጧቸው፤ የዚህ ዓይነት ጽሑፎች ዘመን ከመሻገራቸውም በላይ ሕይወት ይቀይራሉ::
የምስጋና ስጦታ
ሰዎች ለሠሩት ሥራ ወይም ላደረጉት ለውጥ ‹‹ትልቅ ሥራ ሠርተሻል›› ‹‹ዛሬ በጣም አምሮብሃል›› ‹‹በጣም ቆንጆ ምግብ ሠርተሻል››
ወዘተ.. በማለት አድናቆትዎን ይግለጹ ይህን ዓይነት እውነተኛ አድናቆት የሰዎችን ቀን ብሩህ ያደርጋል:: መልካም ውለታ የማድረግ ስጦታ
ከዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎ ወጣ ይበሉና ለሚወዱዋቸው ሰዎች ያልተጠበቀ ድርጊት በመፈጸም ያስደንቋቸው:: አረጋውያንን መጠየቅ፤
ሕፃናትን ማጫወት ወዘተ
የሰላም ስጦታ
ሰዎች ብቻቸውን መሆን በሚፈልጉበት ሰዓት ብቻቸውን እንዲሆኑ በመፍቀድ (በመተው) ሰላማቸውን እንደ ስጦታ ይስጧቸው::
የበጎ ቃላት ስጦታ
መልካም ሰላምታ በመስጠት፤ ለተደረገልዎ ነገር ሁሉ ምስጋና በማቅረብ በመልካም ቃላትዎ የሰዎችን መልካም ስሜት ይጠብቁላቸው::

የሺፒንግና ሎጀስቲክስ ጆርናል (2004)


የሞትና አጋፋሪ እንደሻው ጥንስስ (በ ስብሀት ገብረእግዚአብሄር)
ተረት ሰፈር ስንኖር ሴቶቹ እማሆይ ጣዲቄ የሚሏቸው ባልቴት ነበሩ:: “ያጋፋሪ እንደሻውምንጭ እሳቸው ናቸው፣ እና
በበኩላቸው ከተራው ሰው ለየት ያሉ ናቸው፣ እንደ ገፀ-ባህሪያችን:: ገና ስንነሳ፣ እማሆይ ቢሉዋቸውም መነኩሲት አይደሉም፣ ለማኝ ናቸው:: ነብሳቸው እንደ አጋፋሪነታቸው ተጓዥ በመሆኗ፣ ለልመና ጧት (ለማኝ ሳያራ ሊሆን ይችላል) ኦቶቡስ ተሳፍረው እስከ መጨረሻ ፌርማታ ተጉዘው ይወርዳሉ:: ቀኑን ሲለምኑ ውለው (ትዕዛዙበግንባርሽ ላብ ትበያለሽስለሆነባቸው) በኦቶቡሳቸው ወደ ተረት ሰፈራችን ይመለሳሉ:: ሴቶች በተለያየ አጋጣሚ ለቡና ይጠሩዋቸዋል (ባልተቤቴ ስትልክባቸውጣት የምታስቆረጥምቁርስ ታዘጋጃለች)
ጀበናም ሲወርድ እማሆይ ጣዲቄ የራሳቸውን ሲኒ አውጥተው (ከየት እንዳወጡት አላየሁም) እጃቸውን ሲዘረጉላት፣ ካዳሚዋ ረኮቦቱ ላይ ከመሰሎቹ ሲኒዎች ትደረድረዋለች……. አንድ ከሰዓት በኋላ፣ እማሆይ ጣዲቄ ከሚስቴ ጋር ከቀብር ተመልሰው፣ እጣኑ እየጤሰ ቡናው እየተጠጣ፣ ለረዥም ጊዜ ሳውቃት ሞት በጭራሽ የማያስፈራት ሚስቴውይ ሲያሳዝኑ መሞት እንደዚያ ሲፈሩ መሞታቸው!” ስትል በቁጭትምን ለሳቸው ታዝኛለሽ አሉ እማሆይቀኛዝማች ሳህለ ጆርጊስ አሉልሽ አይደለም?”
(ይኸውላችሁ እንግዲህ አንባብያን ሆይ! አጋፋሪን ፃፋቸው ሲለኝ ይመስላል፣ በዚያች
ደቂቃ “ጆሮዬ ቆመ” - ባህላዊ ጥቅሶቼን እያስተዋላችሁልኝ አደራ)
“ቀኛዝማች ሳህለ ጆርጊስ?” በጉጉት እማሆይ ጣዲቄን ጠየቅኳቸው
“ይኸውላችሁ፣ ዛሬ እዚህ ሊሴ ፈረንሳይ ተማሪ ቤት ያለበት ቦታ፣ በዘበኑ ዙሪያውን
የቀኛዝማች ሳህለ ጆርጊስ ቤተሰቦች ነበረ:: እና እሳቸው ከዘመዶቻቸው ሁሉ የተለየ ሞትን
የመፍራት አባዜ ተጠናውቷቸው ነበር “የትም ሄደው ይመለሱ፣ ከበቅሎዋቸው ሳይወርዱ አሽከሮቹን “ሰፈር ደህና ነው?” ይሉዋቸዋል…”…እንግዲህ ወጣት ደራሲያን “ሞትና አጋፋሪ እንደሻው” እማሆይ ጣዲቄ እንደነገሩኝ ሆኖ (ያውም ቃል በቃል)
የመጀመሪያዋ አረፍተ ነገር ብቻ የኔ ነች (ለትረካው እንዲያመች) ከዚያ የሚቀጥሉት ምዕራፎች (“ቆሪጥና አጋፋሪ…”) እማሆይ
የነገሩኝ እንደ እርሾ እየሆነ፣ እኔ እያቦካሁ እየጋገርኩ፣ ይህ መድበል እንደ አገልግል ተከድኖ ተለጉሞ ደርሷችኋል፣ ለሚቀጥለው የራሳችሁ የፈጠራ ጉዞ እንደ ማደፋፈሪያ እንደ “አይዞን!” ሊሆናችሁ ይችላል በሚል ተስፋ፣ በሄዳችሁበት ይቅናችሁ!
ስብሐት ለአብ ገብረ እግዚአብሔር
ለ “አምስት ስድስት ሰባት” አጭር ልቦለዱ
የፃፈው መግቢያ (2004)

ባዶ ክብር
የገረመኝ መዋሸቱ ሳይሆን ከዚህ በኋላ ላምነው አለመቻሌ ነው:: አንድ ጊዜ አንዲት እውነት ማውራት የማይሆንላት ወጣት፣ እጮኛዋና እርሷ ስላሳላፉት ጥሩ ጊዜ ለጓደኛዋ ስታወራላት እንዲህ አለች፡- ‹‹እጮኛዬ ፓይለት እንደሆነ ታውቂያለሽ
አይደል?›› (ልብ በሉ! ጓደኛዋ ፓይለት አይደለም)::  ‹‹አንድ ቀን በግሉ አይሮፕላን ሊያንሸራሽረኝ ፈልጎ ጠዋት ከቦሌ ተነሥተን እየበረርን ሰበታ አረፍን›› አለቻት:: የምታዳምጣት ጓደኛዋም ‹‹እንዴ!... አንቺ? ሰበታ አይሮፕላን ማረፊያ አለ እንዴ?›› ስትላት ልጅቷም ‹‹ውይ! ሰበታ አልኩ እንዴ ወልቂጤ እኮ ማለቴ ነው›› በማለት ሸመጠጠች፤ አሁንም ጓደኛዋ ‹‹አንቺ! አሁንስ አበዛሽው! ወልቂጤ እኮ አይሮፕላን ማረፊያ የለም!›› ብትላትም ‹‹አይ አይደለም ተሳስቼ ነው ሱሉልታ ማለቴ እኮ ነው›› ብላ የውሸት ድፍረቷን
ቀጠለች:: በዚህ ዓይነት ብዙ ከተሞችን ስትጠራ ከቆየች በኋላ በመጨረሻም አላፈናፍን ያለቻት ጓደኛዋ ‹‹… ዛሬ በሰማይ ላይ ስትበሪ ትቆያለሽ እንጂ አታርፊያትም…›› ብላ ቀለደችባት:: አንዳንድ ጊዜ ብዙ ሰዎች የመዋሸት ምክንያት ሳይኖራቸው ዝም ብለው የሚቀጥፉበት አጋጣሚ አለ:: መዋሸት ግን ከመከበር ይልቅ ያዋርዳል:: በሰዎች ዘንድ ከፍ ከመደረግ ይልቅ በተቃራኒው ሐፍረትን ያከናንባል:: የሰው ክብሩና መመዘኛው ‹‹እኔ እንደዚህ ነኝ!›› ‹‹እንዲህና እንደዚህ ዓይነት ሀብት አለኝ››
የሚለው ባዶ ክብር አይደለም:: ብዙ ጊዜ እንደዚህ ዓይነት የውሸት ተግባራት ከመከበር ይልቅ ውርደትን ያመጣሉ::

በውሸት ራሳችንን ከፍ ስናደርግ ባዶነታችንን ማሳየታችን እንደሆነ ማወቅ አለብን:: አበው ‹‹ባዶ ዕቃ ብዙ ድምጽ ያሰማል!›› ይላሉ:: ባዶ የሆነ ሰው ስለራሱ ብዙ ጉራዎችን መንዛቱ መታወቂያው ነው:: ስለራሳችን ጉራ ስንነዛ ግን ባዶነታችንን ትልቅ ማድረጋችን እንደሆነ እናስተውል:: ፊኛ ትልቅ ቢመስልም በመርፌ ነካ ሲደረግ ግን ውስጡ ባዶ ነው:: ሀሰተኛ ሰውም እንደፊኛ ራሱን ከፍ ቢያደርግም አንድ ቀን በእውነት መርፌ ሲነካ ባዶ መሆኑ ይገለጥበታል:: 
ዳንኤል ዓለሙ (የምሕረት ልጅ) ‹‹ራስን የመለወጥ ምሥጢር›› (2005)

No comments:

Post a Comment